Updated and News Updated and News

የህዝብ ክንፉ መጠናከር ለማኑፋክቸሪንግ እድገቱ ወሳኝ ድርሻ እንደሚወጣ ተጠቆመ

የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ የ2009 ዓ.ም 4ኛውን የህዝብ ክንፍ መድረክ ከሠኔ 05-06/ 2009 ዓ.ም በመቐሌ ከተማ ደስታ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሄደ፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለፁት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሃገሪቱን መፃኢ የኢኮኖሚ ሆኔታ የሚወስን ወሳኝ ዘርፍ እንደመሆኑ ከጅምሩ እያየነው ያለው የባለሀብቱ ተሳትፎ አበረታች መሆኑን ጠቅሠው በቀጣይ ይህንን ተጠቃሚነት ለማጉላት በሚያስችልና የሀገሪቱን እድገት የማስቀጠል አቅም ባለው አግባብ በሠፊው መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አሁን አሁን የማይደፈሩ የሚመስሉ ዘርፎችን ጭምር በመድፈርና በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ ውጤታማ ጅምሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንኑ ጅምር የማስፋት ስራዎች በቀጣይ በተከታታይ እንደሚከናወኑ ገልፀዋል፡፡ ይህ መድረክ የቀጣይዋን ኢትጵዮያ የኢንዱስትሪ ጉዞ መወሰን የሚያስችሉ አቅሞች የተሠባሠቡበት ወሳኝ መድረክ ነው ያሉት አቶ አስፋው ከመድረኩ የሚነሱ ጉዳዮች የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ በመሆናቸው ሁሉም ባለድርሻ ለመድረኩ መጠናከር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ከኢትዮጵያና ከክልል የዘርፍ ማህበራት የተውጣጡ አመራሮች፣ ከወጣትና ሴቶች እንዲሁም ከኣካል ጉዳተኛ ማህበራት እንዲሁም ከፋሽን ዲዛይን ማህበራት የተውጣጡ አካላት የተገኙ ሲሆን ሁሉም የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት አፈፃፀማቸውንና የቀጣዩን በጀት ዓመት እቅዶቻቸውን መሠረት በማድረግ ሠፊ ውይይትን አድርገዋል፡፡

በውይይቱም በወጣት አደረጃጀቶች፣ በገበያና ግብይት፣ በመንግስታዊ አሠራር፣ አደረጃጀትና መመሪያዎች ዙርያ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህም በብድር አሠጣጥ፣ በመስሪያ ቦታ፣ በአመለካከት ዙርያ አሁንም ሰፊ ስራዎችን የሚጠይቁ የቤት ስራዎች እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ይህንን ለማሻሻልም ይህ መድረክ በየወቅቱ ተግዳሮቶቹን በመለየትና በመፈተሽ የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በ06/10/09 በተካሄደው የመስክ ጉብኝት ከመቐሌ ከተማ 50 ኪ.ሜ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሀገረ ሠላም አካባቢ ህ.ወ.ሓ.ት ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ የበላይ አመራሩ አመራር ይሠጥባቸው የነበሩና በህብረተሠቡ ፈቃደኝነት የተሠሩ ዋሻዎች የተጎበኙ ሲሆን በሌላ በኩል በመቐሌ ከተማ በንብ ማጣራትና በተለያዩ ማሽነሪ ስራዎች ላይ የተሠማሩ ኢንዱስትሪዎችን ለመጎብኘት ተችሏል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለፁት በጉብኝቱ የወቅቱ ታጋዮች ይህን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመገንባት የተጓዙበትን አስቸጋሪ የትግል መንገድና የከፈሉትን መስዋዕትነት በአካል በቦታው ተገኝተው ለማየት በመቻላቸው መደሠታቸውን ገልፀው ይህን ያስገኙልንን መልካም አጋጣሚ መሠረት አድርገን በኢንዱስትሪ ልማቱ ላይ የራሳንን አሻራ ለማሳረፍ ትልቅ መነሳሳትን አግኝተናል ብለዋል፡፡የፌዴራል ኤጀንሲው የማኑፋክቸሪንግ አቅም ግንባታ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ካህሠ ገ/መድህን እንደገለፁት በአንድ የትግል ሂደት ውስጥ ለትግሉ ያለ ዕምነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ይህ ትግል ውጤታማ መሆን የቻለውም እነዚህ ጀግኖች በተነሱለት ዓላማ ላይ ያላቸው እምነት ጠንካራ የነበረ በመሆኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ትግል ዘለቄታዊ ውጤታማነት የሃገራችንን ኢንዱስትሪ ልማት እውን በማድረግ ማረጋገጥ እንደሚገባን አሳስበዋል፡፡

Image