Updated and News Updated and News

በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት አምራቾች ብቻ የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር በድምቀት ተከፈተ

በሀገራችን ለ41ኛ ጊዜ የሚከበረውን አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ኢንዱስትሪዎች ብቻ የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር የካቲት 15/2009ዓ/ም በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ በድምቀት ተከፈተ፡፡  

ኤግዚብሽንና ባዛሩን በይፋ የከፈቱት በኢንዱስትሪ  ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አግላቸው አዲስ  ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን  የኢንዱስትሪ  መር ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡  ይህንንም እውን ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍና የሴ ቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ አግላቸው የዚህ ኤግዚብሽንና ባዛርም ዋነኛ ዓላማ ለሴት አምራቾች የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርቶቻቸውን ከመሸጥም ባለፈ ዘላቂ ደንበኞችን እንዲያፈሩ ከማድረጉም በላይ እርስ በርሳቸው በሚፈጥሩት  ትስስር የምርቶቻቸውን ጥራት፣ መጠንና ተፈላጊነት ለማሳደግ ልምድና ተሞክሮ የሚቀስሙበት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው ኤጀንሲው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እድገት ተኮር ተብለው በተለዩ ዋና ዋና ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንሚገኝ ገልፀው፤ ኤግዚብሽንና ባዛሩም ለሴት አምራቾች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል በመፍጠር በዘላቂነት ገበያው የሚፈልገውን ምርት በማምረት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሴቶች ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ የኋላወርቅ እሸቴ በዓለም ለ106ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ ለሴት አምራቾች የገበያ ትስስር ለመፍጠር በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በተጠሪ ተቋማት የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ኢግዚብሽንና ባዛር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም ተሳታፊ ሴቶች ምርቶቻቸውን በመሸጥም ሆነ በማስተዋወቅ እንዲሁም በቀጣይ የተሻለ ምርት ለማምረት እርስ በእርስ ልምድ ሊለዋወጡበት እንደሚገባ መልክት አስተላልፈዋል፡፡

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ ሴት አምራቾች የሚሳተፉ ሲሆን ለ4 ተከታታይ ቀናትም ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

Image